ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዜግነት ግብፃዊ ናቸው በተጋድሎ ኢትዮጵያዊ ናቸው:: ቁጥራቸው ከባሕታዊያን እንደመሆኑና ተጋድሎአቸው በኢትዮጵያ እንደመሆኑ ግብፃውያን ጨርሶ አያውቁአቸውም:: ስለ እርሳቸው ቅድስናም የሚሰሙት ከእኛ አንደበት ነው::
በአንጻሩ እኛም ስለ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ሙሴ ጸሊም የምንሰማው ከግብፃውያኑ አንደበት ነው:: በእነርሱ አንደበት ኢትዮጵያዊው ሲባል ብንሰማም እኛ ግን በለመድንበት ጥቁሩ ሙሴ ብለን መጥራት ይቀናናል እንጂ ኢትዮጵያዊነቱን ብዙም አጉልተን አናነሳሳም::
በዛሬይቱ ኤርትራ ሐማሴን የተወለደው ቅዱስ አብደል መሲህ አል ሐበሺንም እንዲሁ ግብፃውያን የሚያከብሩትን ያህል በኤርትራውያንና በኢትዮጵያውያን እምብዛም አይታወቅም:: ቅዱሳኑ የዚህ ዓለም ስደተኞች መሆናቸውን ስለሚያስተውሉ መነኩሴ ሀገር የለውም ብለው የሔዱበት ሀገር አድርገው ይኖራሉ
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዙሪያቸውን በአንበሳና በነብር ተከብበው የሚሔዱ አባት ነበሩ:: አቡነ አረጋዊን ደግሞ ከዘንዶ ጋር እናያቸዋለን:: (ይህ ነገር ምንድር ነው? ቅዱሳኑ ከአራዊት ጋር ምን አላቸው?
ነገሩ ወዲህ ነው ሰው በጥንተ ተፈጥሮ (before fall) በቅድስና ይኖር በነበረበት በአዳምና ሔዋን ዘመን ከአራዊት ጋር ሰላም ነበረ:: አራዊትን ሳይቀር ያዝዛቸው ያነጋግራቸው ነበረ:: ሔዋን ከዕባብ ጋር በተነጋገረች ጊዜ ዕባብ አፍ አውጥቶ መናገሩ ብርቅ ያልሆነባት ለዚህ ነው:: ሰው ከእግዚአብሔር ሲጣላ ግን የሚፈሩትንና የሚታዘዙለት አራዊት መፍራት ጀመረ::
በሐዲስ ኪዳን የሰውን ክብር ወደ ቀድሞ ሥፍራው የመለሰው ሁለተኛው አዳም መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ግን "በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ ከአራዊትም ጋር ነበረ" ማር 10:13
እኔ ክርስቶስን እመስላለሁ ያለው ጳውሎስም የበረሃ ዕባብ ስትነድፈው ትንኝ እንደነካችው ያህል ምንም ሳይሆን ወደ እሳት አራግፎአት ቁጭ ብሎአል:: በዙሪያው የነበሩ አሕዛብ ከባሕር አደጋ ተርፎ በዕባብ መነደፉን አይተው "ይኼስ ነፍሰ ገዳይ ነው ከባሕር ስንኳ በደህና ቢወጣ እግዚአብሔር በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም" ብለው ከፈረዱበት በኁዋላ ተነድፎ ምንም እንዳልሆነ ሲያዩ ይህስ አምላክ ነው እስከማለት ደርሰው ነበር:: ሐዋ 28:6
ወደ ጥንተ ተፈጥሮ አዳማዊ ቅድስናህ ስትመለስ አራዊት ይገዙልሃል:: ክርስቶስን ስትመስል እንደ አቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሳና ነብር ይሰግዱልሃል::
አንበሳና ነብር ባታገኝ አውሬው ምላስህ አራዊት ምኞቶችህ ይታዘዙልሃል::
"ትሑትና ቅዱስ ሰው በላተኛ አውሬዎችን ሲቀርባቸው ሲመለከቱት አውሬነታቸው ይገራል፡፡ እንደ ጌታቸውም ያዩታል፡፡ በፊቱ አጎንብሰው እግሩን ይልሳሉ፡፡ አዳም በገነት ሳለ ስም ሲያወጣላቸው የነበረውን መዓዛ ከእርሱ ሲወጣ ያሸትታሉ’ ይላል ይስሐቅ ዘነነዌ (Isaac of Nineveh, Ascetical Homilies 77)
ቅዱስ ላሊበላ በአት ላንጽልዎ እያለ እየተማጸናቸው እንቢ ብለው የዝቋላን በረሃ የመረጡት መናኝ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወደ ጥንተ ተፈጥሮ ቅድስና ተመልሰው ከውድቀት ወዲህ የመጣውን የቆዳና የቅጠል ልብስ ሳይሹ በጸጋ እግዚአብሔር በብሩሕ ጠጉር ተሸፍነው ለሀገራችን ጸልየዋል::
ጻድቁ አባታችን አራዊትን በገሠጹበት ጸሎት ዛሬም በሀገራችን የተሠማራውን የጥላቻና የመጨካከን አራዊታዊ ጠባይ ይገሥጹልን::
© ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
✍️ ጥቅምት 5 2013 ዓ ም
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)